13. “ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው።
14. የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ።
15. የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይታረድ።
16. የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ።
17. ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።