1. “ ‘ማንኛውም ሰው የሚያቀርበው ቊርባን ከላሞች መንጋ የሚቀርብ የኅብረት መሥዋዕት ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕት ወይም እንስት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።
2. በሚያቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ይረደው፤ ካህናቱም የአሮን ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት።
3. ከኅብረት መሥዋዕቱ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ ቊርባን አድርጎ ያምጣ፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ በሆድ ዕቃው ላይ ያለውን ሥብ ሁሉ፣
4. ሁለቱን ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አንድ ላይ አውጥቶ ያቅርብ።