ዘሌዋውያን 27:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ አምስት ሰቅል ጥሬ ብር፣ ለሴት ከሆነ ሦስት ሰቅል ጥሬ ብር ይሁን።

7. ሥልሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐሥራ አምስት ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ዐሥር ሰቅል ይሁን።

8. ስእለት የተሳለው ድኻ ከሆነና ግምቱን መክፈል ካልቻለ ግን፣ ለስጦታ ያሰበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የተሳለው ሰው ባለው ዐቅም መሠረት መክፈል የሚገባውን ይተምንለታል።

9. “ ‘ሰውየው የተሳለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ እንስሳ የተቀደሰ ይሆናል።

10. ሰውየው መልካም የሆነውን እንስሳ መልካም ባልሆነው፣ መልካም ያልሆነውንም መልካም በሆነው አይለውጥ ወይም አይተካ፤ አንዱን እንስሳ በሌላው ከተካም ሁለቱ የተቀደሱ ይሆናሉ።

11. እንስሳው በሥርዐቱ መሠረት የረከሰ፣ ለእግዚአብሔርም (ያህዌ) መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይገባው ከሆነ፣ ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያቅርብ፤

12. መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን፣ ካህኑ ዋጋውን ይወስን፤ የካህኑም ውሳኔ የጸና ይሆናል።

13. ባለቤቱ እንስሳውን መዋጀት ከፈለገ ግን፣ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛ መጨመር አለበት።

14. “ ‘አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይሆን ዘንድ ቢቀድስ፣ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን ካህኑ ዋጋውን ይተምን፤ ካህኑም የተመነው ዋጋ የጸና ይሆናል።

15. ቤቱን የቀደሰው ሰው መልሶ ሊዋጀው ከፈለገ ግን፣ የዋጋውን አንድ አምስተኛ በዋጋው ላይ መጨመር አለበት፤ ቤቱም ዳግመኛ የራሱ ይሆናል።

16. “ ‘አንድ ሰው ከወረሰው ርስት ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የዕርሻ መሬት ቢቀድስ፣ ዋጋው የሚተመነው ለመሬቱ በሚያስፈልገው ዘር መጠን ይሆናል፤ ይኸውም ለአንድ ሆሜር መስፈሪያ የገብስ ዘር አምሳ ሰቅል ጥሬ ብር ነው።

17. ሰውየው ዕርሻውን የቀደሰው በኢዮቤልዩ ዓመት ከሆነ፣ የተወሰነው ዋጋ አይለወጥም።

18. ዕርሻውን የሚቀድሰው ከኢዮቤልዩ በኋላ ከሆነ ግን፣ ካህኑ ዋጋውን የሚተምነው እስከሚመጣው የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባሉት ዓመታት ቍጥር ልክ ነው፤ የተተመነውም ዋጋ ይቀነሳል።

ዘሌዋውያን 27