ዘሌዋውያን 27:24-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. በኢዮቤልዩ ዓመትም የዕርሻው መሬት የቀድሞው ባለ ርስት ለነበረው፣ ለሸጠውም ሰው ይመለሳል።

25. እያንዳንዱ ዋጋ የሚተመነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ ሆኖ አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው።

26. “ ‘የእንስሳት በኵር ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ፣ ማንም ሰው የእንስሳትን በኵር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አይችልም፤ በሬም ሆነ በግ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነውና።

27. እንስሳው ርኩስ ከሆነ ግን፣ ባለቤቱ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛ ጨምሮ ሊዋጀው ይችላል፤ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተተመነው ዋጋ ይሸጥ።

28. “ ‘ነገር ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተለይቶ የተሰጠ ማንኛውም ነገር፦ ሰውም ሆነ እንስሳ ወይም በውርስ የተገኘ መሬት አይሸጥም፤ አይዋጅምም። ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ማንኛውም ነገር እጅግ የተቀደሰ ነውና።

29. “ ‘እንዲጠፋ የተወሰነ ማንኛውም ሰው አይዋጅም፤ መገደል አለበት።

30. “ ‘ከዕርሻ ምርትም ሆነ ከዛፍ ፍሬ፣ ማንኛውም ከምድሪቱ የሚገኝ ዐሥራት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነው፤ ለእግዚአብሔርም (ያህዌ) የተቀደሰ ነው።

31. አንድ ሰው ከዐሥራቱ የትኛውንም መዋጀት ቢፈልግ፣ በዋጋው ላይ አንድ አምስተኛ መጨመር አለበት።

32. ከቀንድ ከብቶች፣ ከበጎችና ከፍየሎች መንጋ የሚወጣው ዐሥራት ከእረኛ በትር በታች ከሚያልፉት ዐሥረኛው እንስሳ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ ነው።

33. ሰውየው መልካም የሆነውን መልካም ካልሆነው አይለይ ወይም አይተካ፤ አንዱን በሌላው ቢተካ ግን ሁለቱም እንስሳት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ ሊዋጁም አይችሉም።

34. እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።

ዘሌዋውያን 27