ዘሌዋውያን 27:17-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ሰውየው ዕርሻውን የቀደሰው በኢዮቤልዩ ዓመት ከሆነ፣ የተወሰነው ዋጋ አይለወጥም።

18. ዕርሻውን የሚቀድሰው ከኢዮቤልዩ በኋላ ከሆነ ግን፣ ካህኑ ዋጋውን የሚተምነው እስከሚመጣው የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባሉት ዓመታት ቍጥር ልክ ነው፤ የተተመነውም ዋጋ ይቀነሳል።

19. ዕርሻውን የቀደሰው ሰው መልሶ መዋጀት ከፈለገ፣ በዋጋው ላይ አንድ አምስተኛ መጨመር አለበት፤ ከዚያ በኋላ ዕርሻው እንደ ገና የራሱ ይሆናል።

20. ዕርሻውን ባይዋጅ ወይም ለሌላ ሰው አሳልፎ ቢሸጥ፣ ከዚያ በኋላ ሊዋጀው አይችልም።

21. እርሻው በኢዮቤልዩ በሚለቀ ቅበት ጊዜ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንደተሰጠ ዕርሻ ተቈጥሮ ቅዱስና የካህናቱ ንብረት ይሆናል።

22. “ ‘አንድ ሰው የወረሰው ርስት ያልሆነውን፣ በገንዘቡ የገዛውን የዕርሻ መሬት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቢቀድስ፣

23. ካህኑ የእርሻውን መሬት ዋጋ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ መጠን ይተምናል፤ ሰውየው የተተመነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ አድርጎ በዚያኑ ዕለት ይክፈል።

24. በኢዮቤልዩ ዓመትም የዕርሻው መሬት የቀድሞው ባለ ርስት ለነበረው፣ ለሸጠውም ሰው ይመለሳል።

25. እያንዳንዱ ዋጋ የሚተመነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ ሆኖ አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው።

26. “ ‘የእንስሳት በኵር ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ፣ ማንም ሰው የእንስሳትን በኵር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አይችልም፤ በሬም ሆነ በግ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነውና።

27. እንስሳው ርኩስ ከሆነ ግን፣ ባለቤቱ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛ ጨምሮ ሊዋጀው ይችላል፤ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተተመነው ዋጋ ይሸጥ።

28. “ ‘ነገር ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተለይቶ የተሰጠ ማንኛውም ነገር፦ ሰውም ሆነ እንስሳ ወይም በውርስ የተገኘ መሬት አይሸጥም፤ አይዋጅምም። ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ማንኛውም ነገር እጅግ የተቀደሰ ነውና።

29. “ ‘እንዲጠፋ የተወሰነ ማንኛውም ሰው አይዋጅም፤ መገደል አለበት።

30. “ ‘ከዕርሻ ምርትም ሆነ ከዛፍ ፍሬ፣ ማንኛውም ከምድሪቱ የሚገኝ ዐሥራት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነው፤ ለእግዚአብሔርም (ያህዌ) የተቀደሰ ነው።

31. አንድ ሰው ከዐሥራቱ የትኛውንም መዋጀት ቢፈልግ፣ በዋጋው ላይ አንድ አምስተኛ መጨመር አለበት።

32. ከቀንድ ከብቶች፣ ከበጎችና ከፍየሎች መንጋ የሚወጣው ዐሥራት ከእረኛ በትር በታች ከሚያልፉት ዐሥረኛው እንስሳ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ ነው።

ዘሌዋውያን 27