5. የምትወቁት እህል፣ የወይን ዘለላ እስከምትቈርጡበት ጊዜ፣ የምትቈርጡትም የወይን ዘለላ፣ እህል እስከምትዘሩበት ጊዜ ያደርሷችኋል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
6. “ ‘በምድሪቱ ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ ማንም አያስፈራችሁም። ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም።
7. ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነርሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
8. ከእናንተ አምስቱ መቶውን፣ መቶውም ዐሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
9. “ ‘ፊቴን ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እንድታፈሩና እንድትበዙም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ።
10. የዓምናውን እህል እየበላችሁ ከጐተራው ሳያልቅ ለዘንድሮው እህል ደግሞ ቦታ ታስለቅቃላችሁ።
11. ማደሪያዬን በመካከላችሁ አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም።
12. በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ (ኤሎሂም) እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ።
13. ለግብፃውያን ባሪያዎች እንዳትሆኑ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ፤ የባርነት ቀንበራችሁን ሰብሬ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።
14. “ ‘ነገር ግን ባትሰሙኝ፣ እነዚህን ትዕዛዛት ባትጠብቁ፣
15. ሥርዐቴን ብትንቁ፣ ሕጌን ብታቃልሉ፣ ትእዛዛቴንም ሁሉ ባለመፈጸም ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፣
16. እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና።
17. በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ።
18. “ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤
19. የትዕቢታችሁን ኀይል እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ።
20. ኀይላችሁ በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁ እህሏን፣ የምድሪቱ ዛፎችም ፍሬዎቻቸውን አይሰጡምና።
21. “ ‘በእኔ ላይ ማመፅ ብትቀጥሉና ባትታዘዙኝ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን ሰባት ዕጥፍ መቅሠፍት እጨምርባችኋለሁ።