ዘሌዋውያን 26:29-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. የወንዶች ልጆቻችሁን ሥጋና የሴቶች ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ።

30. የኰረብታ መስገጃዎቻችሁን እደመስሳለሁ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በድኖቻችሁን በድን በሆኑት ጣዖቶቻችሁ ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች።

31. ከተሞቻችሁን አፈራርሳለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም ወና አደርጋለሁ፤ ጣፋጭ ሽታ ያለውን መሥዋዕታችሁንም አልቀበልም።

32. በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁ እስኪደነቁ ድረስ፣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ።

33. በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ሰይፌን መዝዤም አሳድዳችኋለሁ። ምድራችሁ ባድማ፣ ከተሞቻችሁም ፍርስራሽ ይሆናሉ።

34. ምድሪቱ ባድማ በሆነችበት ጊዜ ሁሉና እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር በምትኖሩበት ወቅት ምድሪቱ በሰንበት ዓመቷ ትደሰታለች፤ ምድሪቱም በሰንበቷ ታርፋለች፤ ትደሰታለችም።

35. ምድሪቱ እናንተ በነበራችሁባት ጊዜ በሰንበት ያላገኘችውን ዕረፍት፣ ባድማ በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ ታገኛለች።

36. “ ‘ከእናንተ በሕይወት የተረፉትን፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ድንጋጤ እሰድባቸዋለሁ፤ ነፋስ የሚያንቀሳቅሰው የቅጠል ድምፅ ያስበረግጋቸዋል፤ የሚያሳድዳቸውም ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሮጣሉ፤ ይወድቃሉም።

37. የሚያሳድዳቸው ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት መቆም አትችሉም።

ዘሌዋውያን 26