ዘሌዋውያን 26:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና።

17. በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ።

18. “ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤

19. የትዕቢታችሁን ኀይል እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ።

20. ኀይላችሁ በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁ እህሏን፣ የምድሪቱ ዛፎችም ፍሬዎቻቸውን አይሰጡምና።

21. “ ‘በእኔ ላይ ማመፅ ብትቀጥሉና ባትታዘዙኝ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን ሰባት ዕጥፍ መቅሠፍት እጨምርባችኋለሁ።

ዘሌዋውያን 26