ዘሌዋውያን 26:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ማደሪያዬን በመካከላችሁ አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም።

12. በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ (ኤሎሂም) እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ።

13. ለግብፃውያን ባሪያዎች እንዳትሆኑ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ፤ የባርነት ቀንበራችሁን ሰብሬ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።

14. “ ‘ነገር ግን ባትሰሙኝ፣ እነዚህን ትዕዛዛት ባትጠብቁ፣

15. ሥርዐቴን ብትንቁ፣ ሕጌን ብታቃልሉ፣ ትእዛዛቴንም ሁሉ ባለመፈጸም ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፣

16. እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና።

17. በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ።

18. “ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤

19. የትዕቢታችሁን ኀይል እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ።

20. ኀይላችሁ በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁ እህሏን፣ የምድሪቱ ዛፎችም ፍሬዎቻቸውን አይሰጡምና።

21. “ ‘በእኔ ላይ ማመፅ ብትቀጥሉና ባትታዘዙኝ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን ሰባት ዕጥፍ መቅሠፍት እጨምርባችኋለሁ።

22. የዱር አራዊትን እሰድባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤ ከብቶቻችሁን ያጠፉባችኋል፤ ቊጥራችሁ ይመነምናል፤ መንገዶቻችሁም ሰው አልባ ይሆናሉ።

23. “ ‘በዚህ ሁሉ ግን ወደ እኔ ባትመለሱ፣ በእኔም ላይ ማመፃችሁን ብትቀጥሉ

24. እኔም ጠላት እሆንባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም ሰባት ዕጥፍ አስጨንቃችኋለሁ።

ዘሌዋውያን 26