37. ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት።
38. የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ (ኤሎሂም) ልሆን፣ ከግብፅ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
39. “ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው።
40. በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቊጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤
41. ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ።
42. እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ።
43. በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ።
44. “ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ።
45. እንደዚሁም በመካከላችሁ ከሚኖሩት መጻተኞችና ከተወለዱት ወገናቸው ባሪያዎችን ግዙ፤ ንብረታችሁም ይሁኑ።
46. እነርሱንም እንደ ንብረት ለልጆቻችሁ አውርሷቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ባሪያዎች ይሁኑአችሁ፤ እስራኤላውያን ወገኖቻችሁን ግን በጭካኔ አትግዟቸው።
47. “ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆንና ከወገናችሁ አንዱ ደኽይቶ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ወይም ከመጻተኛው ወገን ለአንዱ ራሱን ቢሸጥ፣
48. ከተሸጠ በኋላ ሊዋጅ ይችላል። ከዘመዶቹም አንዱ፦
49. አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ወይም ከወገኖቹ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ ይዋጀው፤ ሀብት ካገኘም ራሱን መዋጀት ይችላል።
50. እርሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንሥቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር በመሆን ይቊጠር፤ ነጻ የሚለቀቅበትም ዋጋ በእነዚያ ዓመታት ለአንድ ቅጥር ሠራተኛ በሚከፈለው መሠረት ይተመናል።