ዘሌዋውያን 25:35-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. “ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደ ምትረዳ እርዳው።

36. ወገንህ በመካከልህ ይኖር ዘንድ ምንም ዐይነት ወለድ አትቀበለው፤ አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራው።

37. ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት።

38. የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ (ኤሎሂም) ልሆን፣ ከግብፅ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

39. “ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው።

40. በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቊጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤

41. ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ።

42. እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ።

43. በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ።

44. “ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ።

ዘሌዋውያን 25