1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፤
2. “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራስዋ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሰንበት ታክብር።
3. ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ።
4. በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ።
5. ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ።
6. ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋር ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤
7. እንዲሁም ለቤት እንስሶችህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን።