13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
14. “ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው።
15. እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን (ኤሎሂም) ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቶአልና ይጠየቅበታል።
16. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ማኅበሩ ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ከሰደበ ይገደል።
17. “ ‘ሰውን ደብድቦ የገደለ ይገደል።
18. የሌላውን ሰው እንስሳ ደብድቦ የገደለ ማንኛውም ሰው ያንኑ ዐይነት እንስሳ ይተካለት።
19. ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጒዳት ቢያደርስ የዚያው ዐይነት ጒዳት ይፈጸምበት፤
20. ይኸውም በስብራት ፈንታ ስብራት፣ በዐይን ፈንታ ዐይን፣ በጥርስ ፈንታ ጥርስ ማለት ነው። በሌላው ሰው ላይ ያደረሰው ጒዳት በእርሱም ላይ ይድረስበት፤