1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2. “እስራኤላውያን ቀድሰው ለእኔ የለዩትን ቅዱስ መሥዋዕት በአክብሮት ባለመያዝ፣ ቅዱስ ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
3. “እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፣ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ መሥዋዕት ቢቀርብ ያ ሰው ከፊቴ ይወገድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
4. “ ‘ከአሮን ዘር ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበት ወይም ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ማንኛውም ሰው እስኪነጻ ድረስ ቅዱሱን መሥዋዕት አይብላ፤ እንዲሁም በአስከሬን የረከሰውን ነገር ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበትን ሰው ቢነካ፣
5. ወይም በደረቱ የሚሳብ የሚያረክስ ነገርን ወይም የሚያረክስ ማንኛውንም ሰው ቢነካ፣ የቱንም ዐይነት ርኵሰት ቢሆን፣
6. እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።