ዘሌዋውያን 21:14-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ባል የሞተባትን፣ የተፋታችውን ወይም በዝሙት ዐዳሪነት የረከሰችውን ሴት አያግባ፤ ነገር ግን ከወገኖቹ መካከል ድንግሊቱን ያግባ።

15. በወገኖቹ መካከል ዘሩን አያርክስ። እርሱን የምቀድሰው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”

16. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

17. “አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ እንከን ያለበት ማንኛውም ሰው የአምላኩን (ኤሎሂም) ምግብ ይሠዋ ዘንድ አይቅረብ።

18. ዕውር ወይም አንካሳ፣ የፊቱ ገጽታ ወይም የሰውነቱ ቅርጽ የተበላሸ ማንኛውም የአካል ጒድለት ያለበት ሰው አይቅረብ።

19. እንዲሁም እግሩ ወይም እጁ ሽባ የሆነ፣

20. ጐባጣ ወይም ድንክ፣ ማንኛውም ዐይነት የዐይን እንከን ያለበት፣ የሚያዥ ቊስል ወይም እከክ ያለበት ወይም ጃንደረባ አይቅረብ።

21. ከካህኑ ከአሮን ዘር ማንኛውም ዐይነት የአካል ጒድለት ያለበት ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ሊያቀርብ አይምጣ፤ እንከን ያለበት ስለ ሆነ፣ የአምላኩን (ኤሎሂም) ምግብ ለማቅረብ አይምጣ።

22. እርሱም የተቀደሰውንና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የአምላኩን (ኤሎሂም) ምግብ ይብላ።

ዘሌዋውያን 21