ዘሌዋውያን 20:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ሥርዐቴን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

9. “ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል፤ አባቱን ወይም እናቱን ረግሞአልና፤ ደሙ በራሱ ላይ ነው።

10. “ ‘አንድ ሰው ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር፣ አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ይገደሉ።

11. “ ‘አንድ ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም አባቱን አዋርዶአል፤ ሰውየውና ሴትዮዋ ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

12. “ ‘አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሁለቱም ይገደሉ፤ ነውር አድርገዋልና ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

13. “ ‘አንድ ወንድ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ እንደሚፈጽም ሁሉ ከወንድ ጋር ቢፈጽም፣ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋልና ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

14. “ ‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናትዋን ቢያገባ፣ አድራጐቱ ጸያፍ ነው፤ በመካከላችሁ እንዲህ ዐይነት ርኵሰት እንዳይገኝ ሰውየውና ሴቶቹ በእሳት ይቃጠሉ።

15. “ ‘ማንኛውም ሰው ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሏት።

16. “ ‘አንዲት ሴት ወደ እንስሳ ቀርባ ግብረ ሥጋ ብትፈጽም፣ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

17. “ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዶአልና ይጠየቅበታል።

18. “ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጦአልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና፣ ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ።

19. “ ‘ከእናትህም ሆነ ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ የሥጋ ዝምድናን ማቃለል ስለ ሆነ ሁለታችሁም ትጠየቁበታላችሁ።

20. “ ‘ማንኛውም ሰው ከአጎቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አጎቱን አዋርዶአልና ሁለቱም ይጠየቁበታል፤ ያለ ልጅም ይሞታሉ።

ዘሌዋውያን 20