5. በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ጠላት እሆናለሁ፤ እርሱንና ከሞሎክ ጋር በማመንዘር እርሱን የተከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።
6. “ ‘ወደ ሙታን ጠሪዎችና ጠንቋዮች ዘወር በማለት፣ በሚከተላቸውና ከእነርሱም ጋር በሚያመነዝር ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።
7. “ ‘ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝና።
8. ሥርዐቴን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
9. “ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል፤ አባቱን ወይም እናቱን ረግሞአልና፤ ደሙ በራሱ ላይ ነው።
10. “ ‘አንድ ሰው ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር፣ አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ይገደሉ።
11. “ ‘አንድ ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም አባቱን አዋርዶአል፤ ሰውየውና ሴትዮዋ ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
12. “ ‘አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሁለቱም ይገደሉ፤ ነውር አድርገዋልና ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
13. “ ‘አንድ ወንድ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ እንደሚፈጽም ሁሉ ከወንድ ጋር ቢፈጽም፣ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋልና ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
14. “ ‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናትዋን ቢያገባ፣ አድራጐቱ ጸያፍ ነው፤ በመካከላችሁ እንዲህ ዐይነት ርኵሰት እንዳይገኝ ሰውየውና ሴቶቹ በእሳት ይቃጠሉ።
15. “ ‘ማንኛውም ሰው ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሏት።
16. “ ‘አንዲት ሴት ወደ እንስሳ ቀርባ ግብረ ሥጋ ብትፈጽም፣ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
17. “ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዶአልና ይጠየቅበታል።
18. “ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጦአልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና፣ ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ።