14. “ ‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናትዋን ቢያገባ፣ አድራጐቱ ጸያፍ ነው፤ በመካከላችሁ እንዲህ ዐይነት ርኵሰት እንዳይገኝ ሰውየውና ሴቶቹ በእሳት ይቃጠሉ።
15. “ ‘ማንኛውም ሰው ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሏት።
16. “ ‘አንዲት ሴት ወደ እንስሳ ቀርባ ግብረ ሥጋ ብትፈጽም፣ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።
17. “ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዶአልና ይጠየቅበታል።
18. “ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጦአልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና፣ ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ።
19. “ ‘ከእናትህም ሆነ ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ የሥጋ ዝምድናን ማቃለል ስለ ሆነ ሁለታችሁም ትጠየቁበታላችሁ።
20. “ ‘ማንኛውም ሰው ከአጎቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አጎቱን አዋርዶአልና ሁለቱም ይጠየቁበታል፤ ያለ ልጅም ይሞታሉ።
21. “ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጐቱ ርኵሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዶአልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ።
22. “ ‘እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም።
23. ከፊታችሁ የማሳድዳቸውን አሕዛብ ልማድ አትከተሉ፤ እነዚህን ሁሉ በማድረጋቸው ተጸየፍኋቸው።
24. እናንተ ግን፣ “ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ማርና ወተት የምታፈሰውን አገር ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ” አልኋችሁ፤ ከአሕዛብ የለየኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
25. “ ‘ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት እንስሳት እንዲሁም ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት ወፎች መካከል ልዩነት አድርጉ። ርኩስ ነው ብዬ በለየሁት በማንኛውም እንስሳ ወይም ወፍ ወይም በምድር ላይ በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ነገር ራሳችሁን አታርክሱ።
26. እናንተ ለእኔ ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ ነኝና፤ የኔ ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ለይቻችኋለሁ።
27. “ ‘ከመካከላችሁ ሙታን ጠሪ ወይም መናፍስት ጠሪ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት ይገደል፤ በድንጋይም ይወገሩ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’ ”