6. መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግሥቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል።
7. በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም።
8. ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።
9. “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በእርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ።
10. የወይንህን እርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
11. “ ‘አትስረቁ፤“ ‘አትዋሹ፤“ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታል።
12. “ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን (ኤሎሂም) ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
13. “ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤“ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።