ዘሌዋውያን 18:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “ ‘ከእናትህ ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም አባትህን አታዋርድ፤ እናትህ ናት፤ ከእርሷ ጋር በግብረ ሥጋ አትገናኝ።

8. “ ‘ከአባትህ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ አባትህን ያዋርዳል።

9. “ ‘ከእኅትህ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን ከአባትህ ወይም ከእናትህ ሴት ልጅ ጋር በግብረ ሥጋ አትገናኝ።

10. “ ‘ከወንድ ልጅህ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጅህ ሴት ልጅ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ አንተን ያዋርዳል።

11. “ ‘የአባትህ ሚስት፣ ለአባትህ ከወለደቻት ሴት ልጅ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እኅትህ ናት።

12. “ ‘ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የአባትህ የሥጋ ዘመድ ናት።

13. “ ‘ከእናትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የእናትህ የሥጋ ዘመድ ናትና።

14. “ ‘ከአባትህ ወንድም ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም፣ የአባትህን ወንድም አታዋርድ፤ እርሷ አክስትህ ናት።

15. “ ‘ከምራትህ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ከእርሷም ጋር በግብረ ሥጋ አትገናኝ።

16. “ ‘ከወንድምህ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ ወንድምህን ያዋርዳል።

17. “ ‘ከእናቲቱና ከሴት ልጇ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ከወንድ ልጇ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጇ ሴት ልጅ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እነርሱ የሥጋ ዘመዶቿ ናቸው፤ ይህም ጸያፍ ነው።

18. “ ‘ሚስትህ በሕይወት እያለች እኅቷን ጣውንት አድርገህ አታግባት፤ ከእርሷም ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም።

19. “ ‘በወር አበባዋ ርኵሰት ጊዜ ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ወደ ሴት አትቅረብ።

ዘሌዋውያን 18