ዘሌዋውያን 18:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሕጌን ታዘዙ፤ ሥርዐቴንም በጥንቃቄ ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

5. ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ እነዚህን የሚጠብቅ በሕይወት ይኖርባቸዋልና፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

6. “ ‘ማንም ሰው ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ወደ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

7. “ ‘ከእናትህ ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም አባትህን አታዋርድ፤ እናትህ ናት፤ ከእርሷ ጋር በግብረ ሥጋ አትገናኝ።

8. “ ‘ከአባትህ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ አባትህን ያዋርዳል።

9. “ ‘ከእኅትህ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን ከአባትህ ወይም ከእናትህ ሴት ልጅ ጋር በግብረ ሥጋ አትገናኝ።

10. “ ‘ከወንድ ልጅህ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጅህ ሴት ልጅ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ አንተን ያዋርዳል።

11. “ ‘የአባትህ ሚስት፣ ለአባትህ ከወለደቻት ሴት ልጅ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እኅትህ ናት።

12. “ ‘ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የአባትህ የሥጋ ዘመድ ናት።

13. “ ‘ከእናትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የእናትህ የሥጋ ዘመድ ናትና።

14. “ ‘ከአባትህ ወንድም ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም፣ የአባትህን ወንድም አታዋርድ፤ እርሷ አክስትህ ናት።

ዘሌዋውያን 18