ዘሌዋውያን 18:12-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “ ‘ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የአባትህ የሥጋ ዘመድ ናት።

13. “ ‘ከእናትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የእናትህ የሥጋ ዘመድ ናትና።

14. “ ‘ከአባትህ ወንድም ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም፣ የአባትህን ወንድም አታዋርድ፤ እርሷ አክስትህ ናት።

15. “ ‘ከምራትህ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ከእርሷም ጋር በግብረ ሥጋ አትገናኝ።

16. “ ‘ከወንድምህ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ ወንድምህን ያዋርዳል።

17. “ ‘ከእናቲቱና ከሴት ልጇ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ከወንድ ልጇ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጇ ሴት ልጅ ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እነርሱ የሥጋ ዘመዶቿ ናቸው፤ ይህም ጸያፍ ነው።

18. “ ‘ሚስትህ በሕይወት እያለች እኅቷን ጣውንት አድርገህ አታግባት፤ ከእርሷም ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም።

19. “ ‘በወር አበባዋ ርኵሰት ጊዜ ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ወደ ሴት አትቅረብ።

20. “ ‘ከባልንጀራህ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም፣ ራስህን በእርሷ አታርክስ።

21. “ ‘ከልጆችህ ማንኛውንም ለሞሎክ እንዲሠዋ አሳልፈህ አትስጥ፤ የአምላክህንም (ኤሎሂም) ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

22. “ ‘ከሴት ጋር እንደሚደረገው ሁሉ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ይህ አስጸያፊ ነው።

23. “ ‘ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም ራስህን አታርክስ። ሴትም ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ራስዋን አታቅርብ፤ ይህ አስጸያፊ ምግባር ነው።

24. “ ‘ከእነዚህ በአንዱ እንኳን ራሳችሁን አታርክሱ፤ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ በእነዚህ ሁሉ ረክሰዋልና።

25. ምድሪቱም ሳትቀር ረከሰች፤ እኔም ስለ ኀጢአቷ ቀጣኋት፤ ስለዚህ የሚኖሩባትን ሰዎች ተፋቻቸው።

26. እናንተ ግን ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ እናንተ የአገር ተወላጆችና በመካከላችሁ የሚኖሩ መጻተኞች ከእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች ማንኛውንም አትፈጽሙ።

27. ከእናንተ በፊት በምድሪቱ የኖሩ ሰዎች እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ ስለ ፈጸሙ፣ ምድሪቱ ረክሳለች።

28. እናንተም ምድሪቱን ብታረክሷት፣ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እንዲሁ እናንተንም ትተፋችኋለች።

ዘሌዋውያን 18