29. ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በመዳፉ ከያዘው ዘይት የቀረውን በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስ፤
30. ካህኑም ርግቦቹን ወይም የዋኖሶቹን ጫጩቶች የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ይሠዋል፤
31. ከእነዚህም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉ ቊርባን ጋር ያቅርብ፤ በዚህም ሁኔታ ካህኑ ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል።”
32. ተላላፊ የቈዳ በሽታ ይዞት የሚነጻበትን መደበኛ መሥዋዕት ለማቅረብ ዐቅም ላነሠው ሰው ሕጉ ይህ ነው።
33. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
34. “ርስት አድርጌ ወደምሰጣቸው ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፣ በዚያ አገር አንዱን ቤት በተላላፊ በሽታ የበከልሁ እንደሆነ፣
35. ባለቤቱ ወደ ካህኑ ሄዶ፣ ‘በቤቴ ውስጥ ተላላፊ በሽታ የሚመስል ነገር አይቻለሁ’ ብሎ ይንገረው።
36. ካህኑ ወደዚያ ቤት በመግባት በሽታውን መርምሮ ርኩስ መሆኑን ከማስታወቁ በፊት፣ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ይዘዝ፤ ከዚህ በኋላ ካህኑ ወደ ቤቱ ገብቶ ይመርምር።
37. በግድግዳው ላይ ያለውን ተላላፊ በሽታ በሚመረምርበት ጊዜ፣ መልኩ ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት የሚያደላ የተቦረቦረ ነገር በግድግዳው ቢታይ፣
38. ካህኑ ከቤቱ ወደ ደጅ ወጥቶ ቤቱን ሰባት ቀን ይዝጋው።
39. ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቤቱን ለመመርመር ይመለስ፤ ተላላፊው በሽታ በግድግዳው ተስፋፍቶ ቢገኝ፣
40. የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡና ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲጣሉ ይዘዝ፤
41. የቤቱ ግድግዳ በሙሉ በውስጥ በኩል እንዲፋቅና ፍቅፋቂው ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲደፋ ያድርግ።
42. በወጡትም ድንጋዮች ቦታ ሌሎች ድንጋዮች አምጥተው ይተኩ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይምረጉ።
43. “ድንጋዮቹ ወጥተው፣ ቤቱ ከተፈቀፈቀና ከተመረገ በኋላ ተላላፊው በሽታ እንደ ገና በቤቱ ውስጥ ከታየ፣
44. ካህኑ ሄዶ ይመርምረው፤ ተላላፊው በሽታ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ አደገኛ በሽታ ነው፤ ቤቱም ርኩስ ነው።
45. ስለዚህ ቤቱ ይፍረስ፤ ድንጋዩ፣ ዕንጨቱና ምርጊቱ በሙሉ ከከተማ ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ ይጣል።
46. “ቤቱ ተዘግቶ ሳለ ማንኛውም ሰው ቢገባበት፣ ያ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
47. በዚያ ቤት ገብቶ የተኛ ወይም የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ።