24. ካህኑም ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውን የበግ ጠቦትና አንድ ሎግ ዘይት ይቀበል፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዛቸው።
25. ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውንም የበግ ጠቦት ይረድ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ታችኛ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ፤
26. ከዘይቱም ጥቂቱን በግራ እጁ መዳፍ ውስጥ ያፍስስ፤
27. የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጭ።
28. በመዳፉ ከያዘው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የበደል መሥዋዕቱን ደም ባስነካበት ቦታ፣ ይኸውም የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ።
29. ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በመዳፉ ከያዘው ዘይት የቀረውን በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስ፤
30. ካህኑም ርግቦቹን ወይም የዋኖሶቹን ጫጩቶች የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ይሠዋል፤
31. ከእነዚህም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉ ቊርባን ጋር ያቅርብ፤ በዚህም ሁኔታ ካህኑ ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል።”
32. ተላላፊ የቈዳ በሽታ ይዞት የሚነጻበትን መደበኛ መሥዋዕት ለማቅረብ ዐቅም ላነሠው ሰው ሕጉ ይህ ነው።