1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2. “የታመመው ሰው እንዲነጻ ወደ ካህኑ በሚወስዱት ጊዜ ሥርዐቱ እንዲህ ነው፦
3. ካህኑ ከሰፈር ወደ ውጭ ወጥቶ ይመርምረው፤ ሰውየው ከተላላፊ የቈዳ በሽታው ተፈውሶ ከሆነ፣
4. ካህኑ ስለሚነጻው ሰው፣ ለመብላት ከተፈቀደው የወፍ ዐይነት ሁለት ከነሕይወታቸው፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ እንዲያመጣ ይዘዝ።
5. ካህኑም ከወፎቹ አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ።
6. በሕይወት ያለውንም ወፍ ከዝግባው ዕንጨት፣ ደመቅ ካለው ቀይ ድርና ከሂሶጵ ጋር በምንጩ ውሃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከር።
7. ከተላላፊ በሽታ የሚነጻውንም ሰው ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ መንጻቱንም ያስታውቅ፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ውጭ ይልቀቀው።