ዘሌዋውያን 13:9-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. “ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤

10. ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጒሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣

11. ሥር የሰደደ የቈዳ በሽታ ነውና ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ርኩስ መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነም ሰውየውን አያግልለው።

12. “ደዌው በአካላቱ ሁሉ ላይ በመውጣት በሽተኛውን ከራስ ጠጒር እስከ እግር ጥፍር ያለበሰው መሆኑን ካህኑ እስካየ ድረስ፣

13. ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው የሰውየውን ሰውነት ሙሉ በሙሉ ሸፍኖት ከተገኘ፣ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሙሉ በሙሉ ነጭ ስለ ሆነ ንጹሕ ነው።

14. ነገር ግን ቊስሉ አመርቅዞ ቀይ ሥጋ ቢታይበት ርኩስ ይሁን።

15. ካህኑም የተገለጠውን ቀይ ሥጋ በሚያይበት ጊዜ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቀይ ሥጋ ርኩስ ስለ ሆነ፣ ተላላፊ በሽታ ነው።

16. ቀይ ሥጋ ተለውጦ ከነጣ ግን ወደ ካህኑ ይሂድ፤

17. ካህኑም ይመርምረው፤ ቊስሎች ወደ ነጭነት ተለውጠው ከተገኙ፣ የታመመው ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ንጹሕም ይሆናል።

18. “አንድ ሰው በገላው ላይ ዕባጭ ወጥቶ ቢድን፣

19. ዕባጩ በነበረበት ቦታ ላይም ነጭ ዕብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቍቻ ቢታይ፣ ካህኑ ዘንድ ይቅረብ።

20. ካህኑም ይመርምረው፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ የገባ ቢሆን በቦታውም ያለው ጠጒር ቢነጣ፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ።

21. ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጒር በውስጡ ከሌለ፣ ዘልቆ ካልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰባት ቀን ያግልለው።

22. በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ካገኘውም፣ ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚተላለፍ ነው።

23. ቋቍቻው ግን ባለበት ከቈየና ወደ ሌላ ስፍራ ካልተስፋፋ፣ የዕባጩ ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ።

24. “አንድ ሰው እሳት ቈዳውን ቢያቃጥለውና በተቃጠለው ስፍራ ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቍቻ ቢታይበት፣

25. ካህኑ ይመርምረው፤ ቋቍቻው ባለበትም ቦታ ያለው ጠጒር ቢነጣና ከቈዳው በታች ዘልቆ ቢገባ፣ በቃጠሎው ሰበብ ከውስጥ የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው፤ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።

26. ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጒር የሌለበት፣ ከቈዳውም በታች ዘልቆ ያልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው።

27. በሰባተኛው ቀን ካህኑ ይመርምረው፤ በሽታውም በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ቢያገኘው፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።

28. ቋቍቻ ባለበት ከቈየና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ይልቁንም እየከሰመ ከሄደ፣ በቃጠሎው ሰበብ የተከሠተ ዕብጠት ነውና ካህኑ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ የቃጠሎው ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም።

ዘሌዋውያን 13