ዘሌዋውያን 13:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2. “ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቈዳ ላይ ዕብጠት ወይም ችፍታ ቋቍቻ ቢወጣበትና ይህም ወደ ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚለወጥበት ከሆነ፣ ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት።

3. ካህኑም በሰውየው ቈዳ ላይ ያለውን ቊስል ይመርምር፤ በቊስሉ በተበከለው አካባቢ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ተለውጦ ቢያገኘውና ቦታው ጐድጒዶ ወደ ውስጥ ቢገባ፣ ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ ይህን ባወቀ ጊዜ፣ ሰውየው በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ርኵስ መሆኑ ይገለጽ።

4. በቈዳው ላይ ያለው ቋቁቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጒር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው።

5. በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቊስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው።

6. በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቊስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቊስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።

7. ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤

8. ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።

9. “ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤

10. ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጒሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣

11. ሥር የሰደደ የቈዳ በሽታ ነውና ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ርኩስ መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነም ሰውየውን አያግልለው።

12. “ደዌው በአካላቱ ሁሉ ላይ በመውጣት በሽተኛውን ከራስ ጠጒር እስከ እግር ጥፍር ያለበሰው መሆኑን ካህኑ እስካየ ድረስ፣

ዘሌዋውያን 13