ዘሌዋውያን 11:16-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ሰጐን፣ ጠላቋ፣ ዝይ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣

17. ጒጒት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣

18. የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ስደተኛ አሞራ፣

19. ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ።

20. “ ‘ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ።

21. ነገር ግን ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ።

22. ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ።

23. ነገር ግን ክንፍ ኖሮአቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው።

24. “ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኵስ ይሆናል።

25. የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።

26. “ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል።

27. አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኵስ ይሆናል።

ዘሌዋውያን 11