ዘሌዋውያን 1:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ጠራው፤ ከመገናኛውም ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፤

2. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከእንስሳ ወገን መባ በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ፣ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ።

3. “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው።

4. የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል።

5. ወይፈኑን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት።

6. እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው።

7. የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት።

8. ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤

9. አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መባውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።

10. “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን ያቅርብ።

ዘሌዋውያን 1