10. ከዚያም ካህኑ ዕዝራ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ታማኞች አልነበራችሁም፤ በእስራኤል በደል ላይ በደል በመጨመር ባዕዳን ሴቶችን አገባችሁ።
11. አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፤ ፈቃዱን ፈጽሙ፤ በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብና ከባዕዳን ሚስቶቻችሁ ተለዩ።”
12. ጉባኤውም ሁሉ እንዲህ ሲሉ በታላቅ ድምፅ መለሱ፤ “እውነት ብለሃል፤ ያልኸውን መፈጸም ይገባናል።
13. ይሁን እንጂ በዚህ የተሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው፤ ወቅቱም ክረምት ነው፤ ስለዚህ ውጭ መቆም አንችልም፤ ከዚህም በላይ በዚህ ነገር ብዙ ኀጢአት ስለ ሠራን፣ ይህ ጒዳይ በአንድና በሁለት ቀን የሚያልቅ አይደለም።
14. ስለዚህ ሹሞቻችን በማኅበሩ ሁሉ ምትክ መደረግ ያለበትን ያድርጉ። ከዚያም በዚህ የተነሣ የመጣው የአምላካችን ብርቱ ቊጣ ከእኛ እስኪመለስ ድረስ፣ በየከተሞቻችን ያሉ ባዕዳን ሴቶችን ያገቡ ሁሉ በየከተማው ካሉት ሽማግሌዎችና ዳኞች ጋር በተወሰነው ቀን ይምጡ።”
15. ይህንንም ነገር የተቃወሙት ከሜሱላምና ከሌዋዊው ከሳባታይ ድጋፍ ያገኙት የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሕዝያ ብቻ ናቸው።