13. ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም።
14. ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም።
15. እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤
16. እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤
17. እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤“እንደ መልከጼዴቅ ሹመት፣አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።”
18. የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሮአል፤
19. ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቶአል።
20. ይህ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤
21. እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤“ጌታ ማለ፤ዐሳቡንም አይለውጥም፤‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ”