12. ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ።
13. እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው ሰላም አሉት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩ መጻተኞችና እንግዶች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበርና።
14. እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያሳያሉ።
15. ትተውት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው።
16. አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።
17. አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፣ አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤
18. ይህም እግዚአብሔር፣ “ዘርህ በይስሐቅ ይጠራል” ያለለት ነበር።
19. አብርሃም እግዚአብሔር ሙታንን ሊያስነሣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ይስሐቅንም ከሞት የመነሣት አምሳያ ሆኖ አገኘው።
20. ይስሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ዐስቦ ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው።
21. ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ እያንዳንዳቸውን የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩም ጫፍ ዘንበል ብሎ ሰገደ።
22. ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ፣ ስለ እስራኤል ሕዝብ ከግብፅ መውጣት በእምነት ተናገረ፤ ስለ ዐጽሙም ትእዛዝ ሰጠ።
23. ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም።