25. ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና።
26. ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤
27. ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት።
28. ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም።
29. እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ።
30. ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ።