17. እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?
18. ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች እንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ።
19. ለመሆኑ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስቈጣት ነውን? ይላል እግዚአብሔር፤ “ይልቁን ይህን በማድረጋቸው በሚደርስባቸው ዕፍረት የሚጐዱት ራሳቸውን አይደለምን?
20. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ በሰውና በእንስሳ ላይ፣ በዱር ዛፍና በምድር ፍሬ ላይ ይፈሳል፤ ይነዳል፤ አይጠፋምም።”
21. “ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን በሌሎች መሥዋዕታችሁ ላይ ጨምሩ፤ ሥጋውንም ራሳችሁ ብሉ።
22. የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ስለ መሥዋዕቶችና ስለሚቃጠል መሥዋዕት አልተናገርኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም።
23. ነገር ግን ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ መልካም እንዲሆንላችሁም፣ ባዘዝዃችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ አዘዝኋቸው።
24. እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ።
25. አባቶቻችሁ ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በየቀኑ ሳላሰልስ አገልጋዮቼን ነቢያትን ላክሁባቸው።
26. ሕዝቡ ግን አልሰማኝም፤ ልብ ብሎ ለማድመጥም አልፈለገም፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ አባቶቻቸው ከሠሩት የባሰም ክፉ አደረጉ።” ’
27. “ይህን ሁሉ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱ ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፤ አይመል ሱልህም።
28. ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ይህ ሕዝብ አምላኩን እግዚአብሔርን ያልታዘዘ፣ ምክሩን ያልተቀበለ ወገን ነው፤ እውነት ጠፍቶአል፤ ከአንደበታቸውም ሸሽቶአል።