ኤርምያስ 7:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “ ‘እንግዲህ ቀድሞ የስሜ ማደሪያ አድርጌው ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትንም እዩ።

13. እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም።

14. ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ አሁንም ስሜ በተጠራበት ቦታ፣ በታመናችሁበት ቤተ መቅደስ፣ ለአባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ፤

15. ወንድሞቻችሁ የሆኑትን፣ የኤፍሬምን ሁሉ ሕዝብ እንዳስወገድሁ፣ እናንተንም ከፊቴ እጥላችኋለሁ።’

16. “እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም።

17. እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

18. ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች እንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ።

19. ለመሆኑ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስቈጣት ነውን? ይላል እግዚአብሔር፤ “ይልቁን ይህን በማድረጋቸው በሚደርስባቸው ዕፍረት የሚጐዱት ራሳቸውን አይደለምን?

ኤርምያስ 7