ኤርምያስ 7:11-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ስሜ የሚጠራበት፣ ይህ ቤት በእናንተ ዘንድ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፤ የምታደርጉትን ነገር አይቻለሁ ይላል እግዚአብሔር።

12. “ ‘እንግዲህ ቀድሞ የስሜ ማደሪያ አድርጌው ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትንም እዩ።

13. እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም።

14. ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ አሁንም ስሜ በተጠራበት ቦታ፣ በታመናችሁበት ቤተ መቅደስ፣ ለአባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ፤

15. ወንድሞቻችሁ የሆኑትን፣ የኤፍሬምን ሁሉ ሕዝብ እንዳስወገድሁ፣ እናንተንም ከፊቴ እጥላችኋለሁ።’

16. “እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም።

17. እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

ኤርምያስ 7