1. ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤
2. “በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ በዚያም ይህን መልእክት ዐውጅ፤“ ‘እግዚአብሔርን ለማምለክ፣ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሕዝብ ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
3. የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፤ እኔም በዚህ ስፍራ እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ።
4. ይህ ‘የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ’ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ።
5. መንገዳችሁንና ሥራችሁን በእርግጥ ብታሳምሩ፣ በመካከላችሁ ቅንነት ቢኖር፣
6. መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣
7. ለአባቶቻችሁ ለዘላለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው ምድር፣ በዚህ ስፍራ አኖራችኋለሁ።
8. እናንተ ግን፣ ከንቱ በሆኑ የሐሰት ቃላት ታምናችኋል።”