ኤርምያስ 50:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ፣የሚኖርባት አይገኝም፤በቍስሎችዋም ሁሉ ምክንያት፣በባቢሎን የሚያልፍ ሁሉ ይገረማል፤ ያፌዝባታልም።

14. “እናንተ ቀስት የምትገትሩ ሁሉ፣በባቢሎን ዙሪያ ተሰለፉ፤አንዳች ሳታስቀሩ ፍላጾችን ስደዱባት፤ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርታለችና።

15. ከየአቅጣጫው ጩኹባት፤እጇን ትሰጣለች፤ ምሽጓም ይወድቃል፤ቅጥሮቿ ይፈርሳሉ።ይህ የእግዚአብሔር በቀል ነውና፣እርሷን ተበቀሏት፤በሌሎቹ ላይ እንዳደረገችውም አድርጉባት።

16. ከባቢሎን ዘር የሚዘራውን፣በመከር ጊዜ ማጭድ የጨበጠውንም ዐጫጅ አጥፉት፤ከአጥፊው ሰይፍ የተነሣ፣እያንዳንዱ ወደ ገዛ ሕዝቡ ይመለስ፤ወደ ገዛ ምድሩም ይሽሽ።

17. “እስራኤል አንበሶች ያሳደዱት፣የተበተነ መንጋ ነው፤መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ፣ቦጫጭቆ በላው፤በኋላም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣አጥንቱን ቈረጣጠመው።”

18. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁት ሁሉ፣የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ።

19. እስራኤልንም ወደ መሰማሪያው እመልሰዋለሁ፤በቀርሜሎስና በባሳን ላይ ይሰማራል፤በኤፍሬም ተራሮችና በገለዓድም ላይ፣እስኪጠግብ ይመገባል።

20. በእነዚያ ጊዜያት፣ በዚያ ዘመን፣”ይላል እግዚአብሔር፤“የእስራኤል በደል ይፈለጋል፤አንዳችም አይገኝም፤የይሁዳም ኀጢአት ይፈለጋል፤ከቶም የለም፤እንዲተርፉ ያደረግኋቸውን ትሩፋን እምራለሁና።

ኤርምያስ 50