7. ስለ ኤዶም፤የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ጥበብ ከቴማን ጠፍቶአልን?ምክር ከአስተዋዮች ርቆአልን?ጥበባቸውስ ተሟጧልን?
8. ዔሳውን በምቀጣ ጊዜ፣ጥፋት ስለማመጣበት፣እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ፤ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ሽሹ፤ ጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ተደበቁ።
9. ወይን ለቃሚዎች ወዳንተ ቢመጡ፣ጥቂት ወይን አያስቀሩምን?ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፣የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ብቻ አይደለምን?
10. እኔ ግን ዔሳውን አራቍተዋለሁ፤መደበቅም እንዳይችል፣መሸሸጊያ ስፍራዎቹን እገልጣለሁ፤ልጆቹ፣ ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ ይጠፋሉ፤እርሱም ራሱ አይኖርም።
11. ወላጆች የሌላቸውን ልጆችህን ተዋቸው፤ እኔ ለሕይወታቸው እጠነቀቃለሁ፤ መበለቶቻችሁም በእኔ ይታመኑ።”
12. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከጽዋው መጠጣት የማይገባቸው ሊጠጡ ግድ ከሆነ፣ አንተ እንዴት ሳትቀጣ ትቀራለህ? መቀጣትህ አይቀርም፤ መጠጣት ይገባሃል።
13. ባሶራ ፈራርሳ የድንጋጤ፣ የመዘባበቻና የርግማን ምልክት እንደምትሆን በራሴ ምያለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከተሞቿም ሁሉ ለዘላለም ባድማ ይሆናሉ።”
14. ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ሰምቻለሁ፤“እርሷን ለመውጋት ተሰብሰቡ፤ለጦርነትም ውጡ”የሚል መልእክተኛ ወደ ሕዝቦች ተልኮአል።
15. “እነሆ፤ በሕዝቦች መካከል ታናሽ፣በሰዎችም ዘንድ የተናቅህ አደርግሃለሁ።
16. አንተ በዐለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣የተራራውንም ከፍታ የያዝህ ሆይ፤የምትነዛው ሽብር፣የልብህም ኵራት አታሎሃል፤መኖሪያህን እንደ ንስር በከፍታ ቦታ ብትሠራም፣ከዚያ ወደ ታች እጥልሃለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።