ኤርምያስ 49:14-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ሰምቻለሁ፤“እርሷን ለመውጋት ተሰብሰቡ፤ለጦርነትም ውጡ”የሚል መልእክተኛ ወደ ሕዝቦች ተልኮአል።

15. “እነሆ፤ በሕዝቦች መካከል ታናሽ፣በሰዎችም ዘንድ የተናቅህ አደርግሃለሁ።

16. አንተ በዐለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣የተራራውንም ከፍታ የያዝህ ሆይ፤የምትነዛው ሽብር፣የልብህም ኵራት አታሎሃል፤መኖሪያህን እንደ ንስር በከፍታ ቦታ ብትሠራም፣ከዚያ ወደ ታች እጥልሃለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

17. “ኤዶም የድንጋጤ ምልክት ትሆናለች፤ከቍስሎቿም ሁሉ የተነሣ፣በዚያ የሚያልፍ ሁሉ በመደነቅ ያላግጥባታል።”

18. በዙሪያቸው ካሉት ከተሞች ጋር፣ሰዶምና ገሞራ እንደ ተገለበጡ፣”ይላል እግዚአብሔር፤እንዲሁ ማንም በዚያ አይኖርም፤አንድም ሰው አይቀመጥባትም።

19. “አንበሳ ከዮርዳኖስ ደኖች፣ወደ ግጦሽ ሜዳ ብቅ እንደሚል፣እኔም በኤዶም ላይ ድንገት እወጣለሁ፤ ከምድሩም አባርረዋለሁ።የመረጥሁትን በእርሱ ላይ እሾማለሁ፤እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ማንስ ሊገዳደረኝ ይችላል?የትኛውስ እረኛ ሊቋቋመኝ ይችላል?

20. ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶም ላይ ያለውን ዕቅድ፣በቴማን በሚኖሩትም ላይ ያሰበውን አሳብ ስሙ፤ታናናሹ መንጋ ተጐትቶ ይወሰዳል፤በእነርሱም ምክንያት መሰማሪያቸውን ፈጽሞ ያጠፋል።

21. በውድቀታቸው ድምፅ ምድር ትናወጣለች፤ጩኸታቸውም እስከ ቀይ ባሕር ያስተጋባል።

22. እነሆ፤ እንደ ንስር ተወርውሮ ይወርድባታል፤ክንፎቹንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፤በዚያን ቀን የኤዶም ጦረኞች ልብ፣በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ልብ ይሆናል።

23. ስለ ደማስቆ፤“ክፉ ወሬ ሰምተዋልና፣ሐማትና አርፋድ ደንግጠዋል፤እንደ ተናወጠ ባሕርም ታውከዋል፤ልባቸውም ቀልጦአል።

ኤርምያስ 49