9. የባቢሎን መንግሥት የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፤ በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።
10. ንብረት ያልነበራቸውን ድኾች ግን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ በይሁዳ ምድር ተዋቸው፤ በዚያ ጊዜም የወይን አትክልት ቦታና የዕርሻ መሬት ሰጣቸው።
11. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በክብር ዘበኞቹ አዛዥ በናቡዘረዳን በኩል ስለ ኤርምያስ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤
12. “ውሰደውና እንክብካቤ አድርግለት፤ የሚፈልገውን ነገር ፈጽምለት እንጂ አትጒዳው።
13. የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ ዋና አዛዡ ናቡሸዝባን፣ ከፍተኛ ሹሙ ኤርጌል ሳራስር እንዲሁም ሌሎች የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ፣
14. ልከው ኤርምያስን ከዘበኞች አደባባይ አስወጡት፤ የሳፋን ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወደ ቤቱ እንዲወስደው በዐደራ ሰጡት፤ ኤርምያስም በራሱ ሕዝብ መካከል ተቀመጠ።