ኤርምያስ 37:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

7. “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትጠይቁኝ ዘንድ ወደ እኔ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሰራዊት ወደ ገዛ አገሩ ወደ ግብፅ ይመለሳል፤

8. ባቢሎናውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይወጓታል፤ ይዘውም ያቃጥሏታል።’

9. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ባቢሎናውያን በእርግጥ ትተውን ይሄዳሉ’ ብላችሁ አታስቡ፤ አይሄዱምና ራሳችሁን አታታሉ።

10. የሚዋጋችሁን የባቢሎናውያንን ሰራዊት ሁሉ አሸንፋችሁ፣ ቍስለኞች ብቻ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ቢቀሩ እንኳ፤ እነዚህ ሰዎች መጥተው ይህችን ከተማ ያቃጥሏታል።”

11. የባቢሎን ሰራዊት ከፈርዖን ጭፍራ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ከወጣ በኋላ፣

12. ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን ድርሻ ለመካፈል፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ተነሣ፤

13. ነገር ግን ወደ ብንያም በር ሲደርስ፣ የዘበኞች አለቃ የነበረው የሐናንያ ልጅ የሴሌምያ ልጅ የሪያ የተባለው፣ “ከድተህ ወደ ባቢሎናውያን ልትሄድ ነው!” በማለት ያዘው።

14. ኤርምያስም፣ “ሐሰት ነው! ከድቼ ወደ ባቢሎናውያን መሄዴ አይደለም” አለ፤ የሪያ ግን አልሰማውም፤ እንዲያውም ኤርምያስን አስሮ ወደ መኳንንቱ አመጣው።

15. መኳንንቱም እጅግ ተቈጥተው ኤርምያስን ደበደቡት፤ የግዞት ቤትም አድርገውት በነበረው፤ በጸሓፊው በዮናታን ቤት አሰሩት።

16. ኤርምያስም በምድር ቤት በሚገኝ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ ተደረገ፤ በዚያም ረጅም ጊዜ ቈየ።

17. ከዚያም በኋላ ንጉሡ ሴዴቅያስ ላከበትና ወደ ቤተ መንግሥት አስመጣው፤ ለብቻውም ወስዶ፣ “ከእግዚአብሔር የመጣ ቃል አለህ?” በማለት ጠየቀው።ኤርምያስም፣ “አዎን አለ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፈህ ትሰጣለህ” አለው።

ኤርምያስ 37