1. የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ የነበረው ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤
2. “የብራና ጥቅልል ውሰድ፤ ለአንተም መናገር ከጀመርሁበት ከኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት አንሥቶ እስካሁን ድረስ ስለ እስራኤል፣ ስለ ይሁዳና ስለ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የነገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤
3. ምናልባትም የይሁዳ ሕዝብ ላመጣባቸው ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ ሲሰሙ፣ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ክፋታቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”
4. ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራው፤ ባሮክም እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ በብራናው ላይ ጻፈ።
5. ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ አለው፤ “እኔ ተከልክያለሁና ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት አልችልም፤
6. ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደህ፣ በቃል እየነገርሁህ በብራናው ላይ የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን ለተሰበሰበው ሕዝብ አንብብ፤ ከየከተሞቻቸው ለመጡት ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ አንብብ።
7. እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣና መቅሠፍት ታላቅ ስለ ሆነ፣ ምናልባት ልመናቸውን በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”