1. ነቢዩ ኤርምያስ በምርኮ ተወስደው በሕይወት ለቀሩት ሽማግሌዎች፣ ለካህናቱ፣ ለነቢያቱና ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የላከው የደብዳቤ ቃል ይህ ነው፤
2. ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እቴጌዪቱ እናቱ፣ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፣ አናጺዎችና ብረት ቀጥቃጮች ተማርከው ከኢየሩሳሌም ከተወሰዱ በኋላ ነበር።
3. ደብዳቤውንም ከይሁዳ ንጉሥ ከሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር በተላኩት መልእክተኞች በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ላከው፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤
4. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤
5. “ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤
6. አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ።
7. ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።”
8. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤