1. በዚያው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንደ ነገሠ በዐራተኛው ዓመት፣ አምስተኛ ወር፣ የገባዖኑ ሰው የዓ ዙር ልጅ ነቢዩ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለኝ፤
2. “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ የጫነባችሁን ቀንበር እሰብራለሁ፤
3. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መልሼ አመጣለሁ።
4. የይሁዳንም ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣ ሌሎች ከይሁዳ ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱትንም ሁሉ ወደዚህ ስፍራ እመልሳለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ የባቢሎን ንጉሥ የጫነባቸውን ቀንበር እሰብራለሁና።’ ”
5. ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት ቆመው በነበሩት ሕዝብ ሁሉ ፊት፣ ለነቢዩ ለሐናንያ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦
6. “አሜን፤ እግዚአብሔር ያድርገው፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ፣ ተማርከው የተወሰዱትንም ምርኮኞች ሁሉ ከባቢሎን በመመለስ፣ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ቃል ይፈጽም።
7. ነገር ግን ለአንተም ለዚህም ሕዝብ የምናገረውን ቃል ስማ፤