ኤርምያስ 27:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2. እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “የዕንጨት ቀንበር ሠርተህ በጠፍር ማነቆ አያይዘውና በዐንገትህ አስገባው፤

3. ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት ሰዎች በኩል ለኤዶም፣ ለሞዓብ፣ ለአሞን፣ ለጢሮስና ለሲዶና ነገሥታት መልእክት ላክ።

4. ለጌቶቻቸውም እንዲያሳውቁ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለጌቶቻችሁ ይህን ንገሯቸው፤

5. በታላቁ ኀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ምድርን፣ በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎችና እንስሳት ፈጥሬአለሁ፤ ለምወደውም እሰጣለሁ።

6. አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ የዱር አራዊት እንኳ እንዲገዙለት አደርጋለሁ።

7. የእርሱ አገር በተራው ለሌሎች እስከሚገዛበት ጊዜ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ለእርሱ፣ ለልጁና ለልጅ ልጁ ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት እርሱን ይገዙታል።

8. “ ‘ “ነገር ግን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር የማይገዛ፣ ዐንገቱንም ከቀንበሩ በታች ዝቅ የማያደርግ ማንኛውንም ሕዝብ ወይም መንግሥት በእጁ እስከማጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፣ በመቅሠፍትም እቀጣዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤

9. ስለዚህ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያታችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልመኞቻችሁን፤ መናፍስት ጠሪዎቻችሁንና መተተኞቻቸሁን አትስሙ፤

10. ከምድራችሁ እንድትፈናቀሉ፣ እኔም እንዳሳድዳችሁና እንዳጠፋችሁ የሐሰት ትንቢት ይነግሯችኋልና።

ኤርምያስ 27