10. የይሁዳም ባለ ሥልጣኖች ስለ እነዚህ ነገሮች በሰሙ ጊዜ፣ ከቤተ መንግሥት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔር ቤት፣ ‘አዲሱ በር በተባለው መግቢያ ተቀመጡ።
11. ካህናቱና ነቢያቱም ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ፣ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁት ይህ ሰው በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ስለ ተናገረ ሞት ይገባዋል” አሉ።
12. ኤርምያስም፣ ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የሰማችሁትን ሁሉ በዚህ ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እንድናገር እግዚአብሔር ልኮኛል።
13. አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል።
14. ስለ እኔ ከሆነ ግን እነሆ፤ በእጃችሁ ነኝ፤ መልካምና ተገቢ መስሎ የሚታያችሁን ሁሉ አድርጉብኝ።
15. ነገር ግን የሰማችሁትን ይህን ሁሉ ቃል በጆሮአችሁ እንድናገር እግዚአብሔር በእርግጥ ስለ ላከኝ ብትገድሉኝ፣ የንጹሕ ሰው ደም በማፍሰሳችሁ እናንተ ራሳችሁንና ይህቺን ከተማ፣ በውስጧም የሚኖረውን በደለኛ እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ።”
16. ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮአልና ሊገደል አይገባውም” አሉ።