1. “የይሁዳ ኀጢአት በብረት ብርዕ፣በሾለ የአልማዝ ጫፍ፣ ተጽፎአል፤በልባቸው ጽላት፣በመሠዊያቸውም ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል።
2. ልጆቻቸው እንኳ ሳይቀሩ፣በለመለሙ ዛፎች ሥር፣ከፍ ባሉ ኰረብቶችም ላይ ያሉትን፣መሠዊያቸውንና አሼራ የተባለችውን ጣዖት ምስል ያስባሉ።
3. በአገርህ ሁሉ ከተፈጸመው ኀጢአት የተነሣ፣በምድሪቱ ያለህ ተራራዬ፣ሀብትህንና ንብረትህን ሁሉ፣መስገጃ ኰረብቶችህንም ጭምር፣ለብዝበዛ አደርገዋለሁ።
4. በገዛ ጥፋትህ፣የሰጠሁህን ርስት ታጣለህ፤በማታውቀውም ምድር፣ለጠላቶችህ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ለዘላለም የሚነደውን፣የቍጣዬን እሳት ጭረሃልና።”
5. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በሰው የሚታመን፣በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።
6. በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል።