1. እግዚአብሔር፣ “ሄደህ ከተልባ እግር የተሠራ መቀነት ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅበት፤ ነገር ግን ውሃ አታስነካው” አለኝ።
2. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ መቀነቱን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁበት።
3. ለሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
4. “ገዝተህ የታጠቅህበትን መቀነት ይዘህ፣ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያም በዐለት ንቃቃት ውስጥ ሸሽገው።”
5. ስለዚህ እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ኤፍራጥስዠ ሄጄ ሸሸግሁት።
6. ከብዙ ቀን በኋላም እግዚአብሔር፣ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያ እንድት ሸሽገው የነገርሁህን መቀነት አምጣ” አለኝ።
7. እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ፤ መታጠቂያውን ከሸሸግሁበት ቦታ ቈፍሬ አወጣሁ፤ መታጠቂያውም ተበላሽቶ፣ ከጥቅም ውጭም ሆኖ ነበር።
8. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
9. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳን ትዕቢትና የኢየሩሳሌምን እብሪት እንደዚሁ አጠፋለሁ።
10. ቃሌን መስማት እምቢ ብለው በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ ሊያመልኳቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን ጣዖቶች የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝቦች ከጥቅም ውጭ እንደሆነው እንደዚህ መቀነት ይበላሻሉ።