ኢዮብ 6:5-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. የሜዳ አህያ ሣር እያለው፣በሬስ ድርቆሽ እያለው፣ ይጮኻልን?

6. የማይጣፍጥ ምግብ ያለ ጨው ይበላልን?ወይስ የዕንቍላል ውሃ ጣዕም አለውን?

7. እንዲህ ዐይነቱን ምግብ እጸየፋለሁ፤ለመንካትም አልፈልግም።

8. “ምነው ልመናዬ በተመለሰልኝ፤እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ፤

9. እግዚአብሔር አድቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ፣ምነው እጁ በተፈታ!

10. ፋታ በማይሰጥ ሕመም ውስጥ እየተደሰትሁ፣ይህ መጽናኛ በሆነልኝ ነበር፤የቅዱሱን ትእዛዝ አልጣስሁምና።

11. “አሁንም ተስፋ አደርግ ዘንድ ብርታቴ፣እታገሥስ ዘንድ አለኝታዬ ምንድን ነው?

12. የድንጋይ ጒልበት አለኝን?ሥጋዬስ ናስ ነውን?

13. ያልተሳካልኝ ሰው ነኝና፣ራሴን ለመርዳት ምን ጒልበት አለኝ?

14. “ለወዳጁ በጎነት የማያሳይ ሰው፣ሁሉን የሚችለውን አምላክ መፍራት ትቶአል።

15. ወንድሞቼ ግን እንደማያዛልቅ ጅረት፣ለጊዜው ሞልቶ እንደሚፈስ ወንዝ የማይታመኑ ናቸው፤

16. በረዶ በሟሟ ጊዜ ወንዙ ይደፈርሳል፤ዐመዳይም በቀለጠ ጊዜ ይሞላል፤

17. በበጋ ወራት ግን ይጠፋል፤በሙቀትም ጊዜ መፋሰሻው ላይ አይገኝም።

18. ሲራራ ነጋዴዎች ውሃ አጥተው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፤ወደ በረሓም ገብተው ይጠፋሉ።

ኢዮብ 6